ዜና ቤተ ክርስቲያን
በሐምቡርግ ከተማ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ተቋቋመ በፌደራል ሪፑብሊክ ጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አግልግሎትና ሐዋርያዊ ጉዞ ከዕለት ወደ ዕለት እየተጠናከረ በመሄዱ ፱ነኛው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ነሐሴ 24 ቀን 2003 (29.08.2010 ) ዓ.ም. በሐምቡርግ ከተማ ተቃቃመ። በዚህ በሐምቡርግ ከተማ የተቋቋመው ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዓመታት ሲታሰብና ሲደከምበት ኑሮ ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ዓ.ም. ፍጻሜ አግኝቶ በታቦተ ኪዳነ ምሕረት ስም ቤተ ክርስቲያን በመቋቋሙ በሐምቡርግና በአካባቢው የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ምእመናንና ምእመናት እጅግ ደስ ብሏቸዋል። የሰበካ ጉባኤ ያወጣው መርሃ ግብር እንደሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያኑን ባርከው ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን የሚያስገቡት በሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ መሆናቸውን ያመለክት ነበር ይሁን አንጂ ሊገኙ ባለመቻላቸው የደቡብ ምሥራቅ አውሮጳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በቦታው ተገኝተው ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት ቤተ ክርስቲያኑን ባርከው ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን አስገብተዋል። ለበዓሉም ክብር ሲባል በዋዜማው ነሐሴ 23 ቀን 2003 (28.08.2010 )ዓ.ም የአንድ ቀን ዐውደ ጥናት ተዘጋጅቶ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዛት ተገኝተዋል። የዕለቱም ተናጋሪዎች ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀና ዲያቆን ዶ/ር መርሻ አለህኝ ነበሩ። የሁለቱም ተናጋሪዎች ንግግር በውጭ አገር ስላለችው ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያንን ሂደት ላይ ያተኩረ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል. እንዲሁም በወ/ሮ እናትፈንታ አባተ የተዘጋጀው የሥነ ጥበብ ትርኢት በበዓሉ ላይ በተገኙ እንግዶች ተጎብኝቷል። ለበዓሉም ድምቀትን ሰጥቶታል። እንዲሁም ሥርዓተ ቅዳሴው በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተመርቶ እንዳበቃ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መልእክት በአባ ብርሃነ መስቀል ተድላ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ተነብብዋል። ከዚያም ቀጥሎ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ከበርሊን በመመላለስ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡትን አባት አባ ብርሃነ መስቀል ተድላን አመስግነው ታቦተ ሕጉ እስከ ገባ ድረስ ቋሚ ካህን እጅግ አስፈላጊ ሁኖ መገኘቱን አበክረው ተናግረዋል። ለዚህም በሐምቡርግና በአካባቢው የሚኖሩ ምእመናን እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። በሐምቡርግ ከተማ ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም ለ22 ዓመታት የተደረገው ድካም ሁሉ ከፍጻሜ በመድረሱ » አጭሩ ጉዞ በረጅሙ ሲቋጭ» በሚል እፎይታ እስካሁን የተባበሩትን ሁሉ ከልብ አመስግነዋል። ከዚያም በሐምቡርግ ከተማ በተባበሩት የአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት አባል የሆኑት የኤልቢሽ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ተጠሪ ወ/ሮ ካይሰር -ሰቬሪንግ በሐምቡርግ ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን በመቋቋሙ የተሰማችውን ደስታ በራሳቼውና በቤተ ክርስቲያናቸው እንዲሁም በምክር ቤቱ ስም ከገለጹ በኋላ » እንኳን ደስ አላችሁ» ብለዋል ከዚያም አያይዘው ኢየሩሳሌም በነበሩበት ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ የማወቅ ዕድል ስለገጠማቸው »በሐምቡርግ ከተማ አንድ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን መቋቋሙ ለእኛ አንድ ራሱን የቻለ ተጨማሪ በረከት ነው » ብለዋል። በመጨረሻም ታቦተ ሕጉ ወጥቶ ዑደት ከተደረገ በኋላ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ አባታዊ ምክር ሰጥተው ሠርሆተ ሕዝብ ሁኗል። ለበዓሉ የነበረው ዝግጅት ደመቅ ያለ ነበር ከኢትዮጵያኑ ጋር የተጋቡ ጀርመኖችም ያሳዩት የነበረው ትብብር እጅግ መልካም ነበር በተለይም ለልጆች መርሃ ግብር በማዘጋጀት ሐምቡርጎች የታወቁ መሆናቸውን ለመገንዘብ ችለናል። ለወደፊቱ ግን ለመዝሙርም እንደሚያዘጋጅዋቸው ልናሳስብ እንወዳለን / የኮለኘ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሕንጻ እድሳት ተደረገለት የኮለኘ ደብረ ሰላም ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት መቋቋሙ ይታወቃል። በየጊዜው ሲገለጥ እንደ ኖረው ሁሉ ለ12 ዓመት ያህል ተዳብሎ ከኖረ በኋላ ካለው ክርስቲያናዊ ወዳጅነት የተነሣ የጀርመን ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ ለኮለኘ ደብረ ሰላም የኮለኘ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሐንጻ ቤተ ክርስቲያኑን በተውሶ አስረክበው ሂደው ነበር። ምንም እንኳን ከባለቤትነት ያላነሰ አጠቃቀም ቢኖርም በባለቤትነት መያዙ እጅግ አስፈላጊ ሁኖ በመገኘቱ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀና ምእመናኑ ለብዙ ጊዜ ያላሳለስ ጥረት በማድረጋቸው. ከ26 ዓመት በኋላ ደግሞ ለመሸጥና ለመግዛት በተደረገው ስምምነት መሠረት በ2009/2002 ዓ.ም. ግዡ ተካሂድዋል። ይሁን እንጂ በባለቤትነት ከተረከቡ በኋላ እድሳት ማድረግ ተገቢ ሁኖ በመገኘቱ ያካባቢው ምእመናን በአንድ ላይ ተሣሥተው ሙሉ እድሳት እንዲደረግለት አድርገዋል። የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ከዕለት ወደ ዕለት እየተጠናከረ በመሄዱ የምዕመናኑ እንቅሰቃሴ ከማናቸውም ጊዜ ላቅ ባለ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ከዚህም የተነሣ ለእድሳቱ ሥራ በጉልበትና በገንዘብ የተባበሩ እጅግ ብዙዎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። እንዲያውም በቁጥር አንሰተኞች ቢሆኑም ከመቶ አሥር የሚያዋጡ በመገኘታቸው የእድሳቱን ሥራ ለማጠናቀቅ እንደሚቻል ለማወቅ ተችሏል። የእድሳቱን ሥራ ያለምንም ክፍያ ያከናወነው የሥራ ተቋራጭ የሆነው አቶ ቴዎድሮስ ገብረ ሕይወት ሲሆን ጊዜውንና መሣሪያውን በሥራ ላይ ከማዋሉ ባሻገር የቅርብ ወዳጆቹን ይዞ የሠራው ሥራ በቃል የሚገለጽ አይደለም። ለዚህም ወጣት ባለሙያ ያለን አክብሮት እጅግ ከፍ ያለ ሲሆን ከጎኑ ሳይለዩ የተባበሩትን ሁሉ እናመሰግናለን። እንዲሁም እናቶችና እኅቶች እህል ውኃ በማቅረብ ያደረጉት አስተዋጽዖ ምንጊዜም የሚዘነጋ አይደለም። እጅግ ሰላምና ፍቅር የሰፈነበት የሥራ ጊዜ እንደነበር ከተካፋዮቹ ሁሉ በየጊዜው እንደተሰማ ነው። ለብዙ ጊዜ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ለተመላለሱት ደግሞ በተደረገው የእድሳት ሥራ እየተደመሙ ህልም እንጂ እውነት መስሎ እስካሁን እንደማይታያቸው ከአንደበታቸው ለመስማት ተችሏል። ከዚህም የተነሣ ለኮለኘ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እንደ ገና መልካም ጅምር እንላለን። ከእድሳቱ ሥራ ባሻገር የዛፍ ቆረጣ፥ የሣርና የእክልት ተከላ ተካሂዿል። ዐጸደ ቤተ ክርስቲያኑ በበጋ ጊዜ ሊቀቁኘ የማያሰይ ሁኗል። በአዳራሹ ጀርባ የተሠራው ዛኒጋባ ደግሞ ለዕቃዎች ማስቀማጫ ስለ ዋለ በመጠኑም ቢሆን የቦታ ጥበትን ሊቀንስ ችሏል። የቤተ ክርስቲያን የግዥና የሽያጭ በዓል በከፍተኛ ድመቀት ተከበረ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን በአጽመ ርስተነት የምትጠቀምበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ባለፈው ዓመት በ2009/2002 መግዛቷ ይታወቃል። በተላያዩ የመገናኛ አውታርችም መሰራጨቱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ግዡ እንደ ተከናወነ የውስጥ የውኃ መስመር ተሰብሮ በአዳራሹና በወጥ ቤቱ ላይ ርጥበት በማድረሱ የርክክቡ ሥነ ሥርዓት እንዲዘገይ ተደርጎ ነበር። በዚህ ዓመት ግን ከአዲስ ዓመቱ ክብረ በዓል ጋር መስከረም አንድ ቀን 2003/ 09. 11.2010 ዓ. ም. እጅግ ደማቅ በሆነ መልኩ ተከብሮ ውሏል። በክብረ በዓሉ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና የመንግሥት ተጠሪዎች ተገኘተዋል። የኮለኘ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መዘምራንም በቤተ ክርስቲያኑ በር ባለው ዐውደ ምሕረት በእምመናኑ ታጅበው ፣ቀኝና ግራ በመቆም ከበሮው እተየጎሰመ መዝሙር እየተዘመረ ለክብር እንገዶች ያደረጉት አቀባበል እጅግ ደማቅ ነበር። የርክክቡ ክብረ በዓል የገዥዎችና የሻጮች እንደ መሆኑ መጠን በጋራ ጸሎት እንዲከናወን ሁኗል። የጸሎቱ መርሃ ግብር እንዳለቀ መዘምራኑ የተላያየ ጣዕመ ዝማሬ ያላቸውን መዝሙሮች አቅርበዋል። ከዚያም ሊቀ ካህናት ዶ/ መርዓዊ ተበጀ እድምተኞቹን እንኳን ወደ »ምድረ ኢትዮጵያ» በሰላም መጣችሁ በማለት አጠር ያለ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸው በአጽንኦት የተናገሩት ቢኖር ለ26 ዓመታት » ሰው ያስባል፧ እግዚአብሔር ይፈጽማል» በሚል መርህ እጅግ ቁጠባ በሞላበት ሂደት በተሰበሰበ ገንዘብ የተጋዛ መሆኑ ነው። ያለ ማቋረጥ የተባበሩትን ሁሉ አመስግነው የማይቻለውን እንዲቻል ላደረግ ልዑል እግዚአብሔር ጥልቅ ምስጋና አቅርበዋል። ከዚያም የተለያዩ የክብር እንግዶች የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር አድርገው እንዳበቁ የክብረ በዓሉ የክብር ተናጋሪ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ልዑል ዶ/ር አስፋው ወሠን አሥራተ ነበሩ። እርሳቸውም »Die Äthiopisch-Orthodoxe Kirche -Ein Hort der äthiopischen Kultur » የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ የባህል ቦታ ናት በሚል ርእስ ንግግር አድርገዋል። ዶ/ር አስፋው ወሠን አሥራተ በንግግር ማራኪነታቸውና በደራሲነታቸው የታወቁ ምሁር በመሆናቸው የአድማጮቻቸውን እዝነ ልቡና እጅግ ማርከውት ነበር። በዓሉ ከአዲስ ዓመት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለምእመናኑ እጅግ ተደራራቢ የደስታና የሰላም ክብረ በዓል ነበር ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ከመላው ጀርመን ማለት ይቻላል ከተለዩ ቦታዎች የመጡ መመናንና መእመናት ተገኝተዋል። ከአባቶችም መካከል መልአከ ብርሃን መስፍን ገብረ ማርያምና መልአከ ፀሐይ አባ ሲራክ ወልደ ሥላሴ የደስታው ተካፋዮች ሁነዋል። የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ለረጅም ጊዜ የዘጋጀበት በመሆኑ ዝግጅቱ ይህ ቀረሽ የሚባል አልነበረም። ጠጁም ተጥሎ ቀርቧል። በዓሉ ለሁለት ቀን የቀጠለ በመሆኑ ሁሉም ሙሉ ነበር። ታዳሚው ሕዝበ ክርቲያን የአገሩን አዲስ ዓመት፥ እንቁጣጣሽን፥ ቅዱስ ዮሐንስን እያስታወሰ »አብሮ የበላ ንቅዱስ ዮሐንስ» አሽረውም የሚለውን የወላጆቹን ብሂል እያሰጋተባ ከብረ በዓሉን ሁለት ቀን ሙሉ በደመቀ ሥነ ሥርዓት አክብሮታል። በየሳምንቱ እሁድ ቡና በማፍላት የምታገኘውን ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያኑ ገቢ የምታደርገው እማማ ላቀች ተገኝ ግን ሁለት ቀን ሙሉ ያፈላችውን ቡና ሽጣ ያገኘችውን አያሌ ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያኑ ገቢ አድርጋች። በተለይም መዘምራን አበበዬ ሆዬን በመዘመር ከ1000,-ኤውሮ በላይ ገቢ አድርገዋል። እዲሁም ኅፃናቱ ደግሞ የእንቁጣጣሽ ሥዕል ለወላጆች በማበርከት ገነዘብ አሰባስበዋል። መቼም በየጊዤው ቤተ ክርስቲያን መግዛት አይቻልም እንጂ ከነበረው ደስታና ፍቅር የተነሣ ጣመኝ ድገመኝ የሚያሰኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ጊዜ ለሌሎቹም የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የምንመኘው የራሳቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ኑሯቸው ያለምንም ሰቀቀን የአምልኮት ተግባራቸውን እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ደብና ትውፊት እዲያካሂዱ ነው። የኮለኙም ራእይ እውን የሆነው ከ26 ዓመት በኋላ ነውና ያለምንም መሰላቸት ሕዝበ ክርስያኑን መቀስቀስ ይገባል እንላለን። በጎ አድራጊዋ አረፉ ከዚህ ቀጥሎ የምናቀርብላችሁ ዜና ከምንጊዜውም ለየት ያለ ነው። በልጅነት ስማቸው አደልሃይድ ኢንግሪድ ስኪልባ ( Adelheid Ingrid Skielwa) ተብለው ይጠሩ ነበር። የተወለዱት እ.አ.አ. 11.6.1941 ነው። ይኸውም የሁለተኛ ዓለም ጦረት የተጀመረበት ዓ.ም. ነበር። ያውም የተወለዱት ሽሌስያ ተብሎ በሚጠራው በአሁኑ ጊዜ በፖላንድ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ክፍለ አገር ነው የጀርመን ናዚ ወታደር ድል ሁኖ፧ የጀርመን ተወላጅ የሞተው ሙቶ የቀረው ሲሰደድ የአምስት ዓመቷ አደልሃይድ ከእናቷ፥ ከእኅቷና ከወንድሟ ጋር ወደ ምዕራብ ጀርመን ተሰዳ ትገባለች። ጊዜው የቀውጢ ዘመን በመሆኑ ብዙ እንግልት ደርሶባታል። ይሁን እንጂ ጀርመን ከጦርነቱ ማጥ ስታገግም የአደልሃይድ ቤተ ሰብም የተደላደለ ኑሮ መኖር ጀመረ። እርሷም ትምህርቷን አጠናቃ ሥራ ያዘች። በዚህም ጊዜ ከዶ/ር ክፈለው ዘለቀ ጋር ሕጋዊ ጋብቻን መሥርታለች። ዶ/ር ክፈለው ዘለቀ ደግሞ በሰላሌ አውራጃ እ.አ.አ. በ 1933 ዓ.ም. ከአንድ ካህን ቤተ ሰብ ተወለዱ̎።፡እኒህ ሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጅ ስለ ሆኑ በመጀመሪያ ወደ ግሪክ ለከፈተኛ መንፈሳዊ የነገረ መለኮት ትምህርት ከተላኩት ወጣት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነበሩ። በአቴንስ ዩኒቬርሲቲ የዶክትሬት መዓርጋቸውን እንዳገኙ ወደ ኢትዮጵያ አልተመለሱም። በፕሮፌሰር ሃየር በኩል የነጻ ትምህርት ዕድል እንዳገኙ ወደ ጀርመን ይመጣሉ። ከዚህ ላይ ነው ከወጣቷ አደልሃይድ ጋር የተጋቡት። እነዚህ ጣምራዎች ለብዙ ̎ዓመታት በፍቅርና በመካበር አብረው ኑረዋል። አደልሃይድ ስኪልቫ እየተባሉ መጠራታቸውን ትተው የባላቸውን አባት ስም በመውረስ ወ/ ሮ ዘለቀ እየተባሉ ይጠሩ ነበር። ዶ/ር ክፈለው ዘለቀ በ1990/ 1998 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ወ/ ሮ አደልሃይድ ዘለቀ ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለ ግንኑነታቸውን አላቋረጡም። በተለይም በረሃቡ ጊዜ በነፍስ አድን ዘመቻው ሙሉ ትብብር ከማድረጋቸውም ሌላ በየጊዜው ለቤተ ክርስቲያናችን ከፈተኛ እገዛ ሲያደርጉ ኖረዋል። ሞንም ደግና ርኅሩኅ ቢሆኑ ከሞት አይቀርምና፧ ወ/ ሮ አደልሃይድ ዘለቀ በተወለዱ በ68 ዓመታቸው ጥቅምት 21 ቀን 2009 AACHEN ከተማ አርፈው የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ደግሞ በቬና ከተማ ኅዳር 3 ቀን 2009 ዓ,ም. ተፈጽሟል። በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ታላቅ ደጋፊ ሴት አጥታለች። ስማቸው ግን ከመቃብር በላይ ይውላል። ወደ ሞት አፋፍ ሲሄዱ እንኳን በአደረጉት ኑዛዜ 5.000,-e ገቢ ሁኗል። ቸሩ አምላካችን የሟችዋን ነፍስ በአብርሃም፤ በይስሐቅና በያዕቆብ አጠገብ ያስቀምጥልን። |