ቤተ ክርስቲያን የማን ናት?

ቤተ ክርስቲያን የማን ናት ወደሚለው ጥያቄ ውስጥ ገብተን አንዳንድ ሆኔታዎችን ከመመልከታችን በፊት በዚህ ዘመን ወይም በዚህ ጊዜ ላለን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች አስቸጋሪ ሆኖ የተገኘው የመደማመጥና የመከባበር ብሎም የመተራረም ባህላችን እየተዳከመና እየተሸረሸረ የሄደ ስለመስለኝ አንዳንድ ሁኔታዎችን ለመጠቃቀስ ስለ ፈለግሁ መሆኑን በቅድሚያ ላስገነዝብ እወዳለሁ።

ቤተ ክርስቲያን የማን ናት? ቤተ ክርስቲያን የማን ናት ወደሚለው ጥያቄ ውስጥ ገብተን አንዳንድ ሆኔታዎችን ከመመልከታችን በፊት በዚህ ዘመን ወይም በዚህ ጊዜ ላለን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች አስቸጋሪ ሆኖ የተገኘው የመደማመጥና የመከባበር ብሎም የመተራረም ባህላችን እየተዳከመና እየተሸረሸረ የሄደ ስለመስለኝ አንዳንድ ሁኔታዎችን ለመጠቃቀስ ስለ ፈለግሁ መሆኑን በቅድሚያ ላስገነዝብ እወዳለሁ።

ቤተ ክርስቲያን የማን ናት በሚለው አንጻር፧ ቤተ ክርስቲያን ምን ናት ለሚል ጠያቄ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚናገረው የሕግ መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በፍትሕ መንፈሳዊ በመጀመሪያው አንቀጽ በቁጥር ፩ ላይ » ቤተ ክርስቲያንሰ ቤተ ጸሎት ይእቲ።» ቤተ ክርስቲያንስ የጸሎት ቤት ናት። ይላል (ማቴ.21,13, ማር.11,17) የፍትሐ ነገሥቱ አዘጋጅ በውስጥዋ የሚፈጸመውን ድርጊት ለመግለጽ ሲል “ ቤተ ክርስቲያንሰ ቤተ ጸሎት ይእቲ።” ቤተ ክርስቲያንስ የጸሎት ቤት ናት አላት እንጂ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ሥርዎ መሠረታዊ በሆነ ገጸ ምንባብ ሲጠናና ሲመረመር ግን ከጸሎት ቤት ባሻገር ማኅበር ወይም ጉባኤ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህንም ሊያረጋግጥልን የሚችለው በሕያው ወልደ እግዚአብሔር ልጅ በመሲሁ በኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ቃል በፊልጶስ ቂሳርያ ለሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ » እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ፧ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ። የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።» ብሎ የተናገረው ነው። (ማቴ.16,18) ይህን መለኮታዊ ሥልጣን ከጌታውና ከመምህሩ የተቀበለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም በክርስቶስ ክርስቶሳውያንና ክርስቶሳውያት የሆኑት ሁሉ አንድነትና ኅብረት ቤተ ክርስቲያን ተብሎ እንደሚጠራ ሲያረጋግጥ » ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን፧ ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል» ይላል። (1.ጴጥ.5፧13) ስለዚህም ነው አባቶቻችን ከሌሎች ቋንቋዎች ሁሉ ለየት ባለ መልኩ በባለቤትና በተዛራፊ መንገድ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስም ሰጥተዋት የምናገኘው። » ቤተ እግዚአብሔርም » ብለው ይጠሯታል። እንግዲህ ማኅበርና ጉባኤ የሚለውንም ያጠቃልላል ማለት ነው። ማኅበርና ጉባኤ በሚለው ውስጥ ደግሞ ከፓትርያርክ እስከ አጻዌ ሆኅት (ቁልፍ ያዥ) ከምእመናን እስከ ምእመናት፧ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያለውን ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ ያጠቃልላል። ታዲያ እንዲህ እስከሆነ ድረስ ቤተ ክርስቲያን የማናት የሚለውን ጥያቄ የሁላችን ናት በሚል መልስ አጠቃሎ፧ ይህን ጽሑፍ ከዚህ ላይ በአጭሩ መቋጨት በተገባ ነበር፧ ለዚህ ጽሑፍ ግን እንደ መግቢያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።

ቤተ ክርስቲያን በግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ተመሥርታ፧ በግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እየተመራች በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻ እነሆ ሁለት ሽህ ዘመን አስቆጥራለች። መሥራችዋ ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ፧ ይህንንም የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም አሳልፎ የሚኖር ልዑል አምላክ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን በሥነ ሥርዓት እንድትመራ ለጠባቂዎች አደራን ሰጥቷል። ከዚህ ላይ የሐዋርርትን ሥልጣን ልብ ይሏል። ለሁሉም ሥልጣን ቢሰጥም ከመካከላቸው ግን ሊቀ ሐዋርያት የተባለው አንዱ የዮና ልጅ ስሞን ጴጥሮስ ነበር። ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ ግን የተለያዩ ሊቃነ መናብርት ሰለ ተቋቋሙ ከዚህ ላይ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ መግባት ብዙ ገጾችን የሚወስድ በመሆኑ እንዲሁ አልፌዋለሁ።

ከላይ በመግቢያው የቤተ ክርስቲያንን ማንነት ለመግለጽ ማኅበር ወይም ጉባኤ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል ብለናል። ማኅበርና ጉባኤ የሚባሉ ነባራውያንን ነገሮች እስካሉ ድረስ ውጥቅጥነቱም በዚያው ልክ እየሰፋ መሄዱ አልቀረም። በተለይም ስብከተ ወንጌል እየተስፋፋ ሲሄድ፧ ሕዝብና አሕዛብ በአንድ ማኅበርና ጉባኤ ውስጥ ሲቀላቀሉ ለጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያንም አንድ ፈታኝ ጉዳይ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ወደ ደማስቆስና ወደ አንጾኪያ ከዚያም ወደ ታናሹ ኤሲያና ወደ ግሪክ ለወንጌል አገልግሎት ተጉዞ ማኅበረ ክርስቲያንን መሥርቷል። ይሁን እንጂ የሚያምኑት ከማያምኑት፧ ክርስቲያኖቹ ከአረማውያኑ፧ ሕዝቡ ከአሕዛቡ ጋር ብቻ ሳይሆን የሚያምኑት ከሚያምኑት፧ ክርስቲያኖቹ ከክርስቲያኖቹ፧ ሕዝቡ ከሕዝቡ ጋር በአረማውያን ዳኞች ላይ መሟገትና መካሰስ ጀመሩ። ይህም ሁኔታ ለቅዱስ ጳውሎስ እንደ ዘመኑ አነጋገር » የራስ ምታትና የልብ ቁስል » ሁኖበታል ማለት ይቻላል። በአሕዛብ አገር በቆሮንቶስ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ሲጽፍ እንዲህ ይላል። » ከእናንተ አንዱ ከባልጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በመፋረድ ፈንታ በዓመጸኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ፧ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፧ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን?። እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበድሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ፧ ታታልሉማላችሁ፧ ያውም ወንድሞቻችሁን።» (1. ቆሮ.6፧ 1-7)

የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ተብሎ የሚጠራው ቅዱስ ጳውሎስ » በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? » በማለት የቆሮንቶስን ምእመናን ይማጸናል። ይህን መሠረታዊ የሆነ ጥያቄ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን መለስ አድርገን ባሁኑ ጊዜ እርስ በእርስ ብንጠያየቅ አንዱ በአንዱ ላይ እጣትን ከመቀሰር አልፎ » ፍረዱልኝ ወይም ፍረዱብኝ » የሚል ማንም አልተገኘም። ከዚህ ላይ » ፍረዱልኝ ወይም ፍረዱብኝ » የሚል ኃይለ ቃል ያነሣሁበትን ምክንያት ልገልጽ እወዳለሁ። በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ሊፈጸሙ የማይገባቸው ድርጊቶች ሲፈጸሙ፧ በዐውደ ምሕረት ነፍስ ሲጠፋ፧ ተቃዋሚ የተባሉ አባቶች ቤት በመንፈቀ ሌሊት ሲደፈርና ብፁዓን አባቶ ሲንገላቱ፧ ሥርዓተ አልበኝነት ሲስፋፋ፧ በመንበረ ፓትርያርክ ዙሪያ አውልዳዮችና ዋልጊዎች ሲበራከቱ፧ የላይ ፈሪ፧ የታች ፈሪ ባዮች ሲበዙ፧ ያለምንም ማስረጃ የግለሰቦች ስም ሲጠፋ፥ በክርስቶስ ምሳሌ በመንበሩ የተቀመጡ ተወጋግዘው ሲያወጋግዙን፥ ብሎም አንዲቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በውግዘት ስትለያይ፧ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሲጣስ እናት ቤተ ክርስቲያን አሁንም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ » በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? » ትለናች። ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሁኔታዎችን በተራ ቁጥር ልገልጽ እወዳለሁ።

1.በቤተ ክርስቲያን ውስጥ “ተላላፊ በሽታ” ገብቷል።
ይህ ጊዜ የማይሰጥ በሽታ ከታውቀበት ግን በቀላሉ አክሞ ለማዳን ይቻላል፧ መድኃኒቱም ቤተ ክርስቲያን የሁላችን ናት ብለን ስንነሣ ብቻ ነው። ይህም ማለት ሁሉ አለቃ ነው ማለት ሳይሆን ሁሉም ድርሻውን ይወጣ ለማለት ነው።

2. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገለልተኛ የሚል ትውፊት ወይስ ሥሪት አለን?

እኛ ክርስቲያኖች የክርስቶስ አካል ነን ብለን ካመን ራስ እግር፧ እግር ራስ፧ ዓይን አፍንጫ፧ አፍንጫ ዓይን ሆኖ አያውቅም ዕድሜ ለፋና ወጊው አባት እንጂ በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካው ቦርድና የገለልተኞ ካህናት ማኅበር ቤተ ክርስቲያንን ወደ ማያስፈልግ ትውፊት ይዟት እየገባ ነው። በሌሎች ቦታዎችም ለማቆጥቆጥ ሙከራው ይታያል። አሁንም » ፍረዱልኝ ወይም ፍረዱብኝ » የሚል ስለ ጠፋ ነው። ከዚህ ላይ ያው የተለመደ አዝማቼን ላስገባና » በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? »

3. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማን ጻፈሽ እንጃ ትውፊታዊ ነውን?
ከዚህ ላይ ባለ ዘመኔ፧ ዕድሜ ልኬን የማስታውሰን በዘመነ ድረ ገጽ እንደ ገና ላስታውሰው ወደድሁ። እንደ እኔ የሰማችሁ ካላችሁም አብረን እናስታውሰው። በልጅነት አእምሮ ስለሆነ ምንም አረሳሁትም በተወለድኩበት ኩታ ገጠም ቤተ ክርስቲያን ብዙ ደብተራዎች ነበሩ። በተለይም አንዱ ከሌሎቹ ሁሉ ለየት ያለ ሰው መሆኑንም በሚገባ አስታውሳለሁ። በዚያ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ያንድ ቤተ ሰብእ ልጅ ተፈነገለ፣ የዘመኑ አነጋገር ነው። ሆኖም ተሠረቀ ለማለት ነው፣ ያን ልጅ ፈንግሎ የሸጠውን ለማወቅ ብዙ ሙከራ ተደረገ፧ ግን ምን ይሆናል ለማወቅ አልተቻለም። ከዕለታት በአንድ ቀን ግን በዐጸደ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ልጁን ፈንግሎ የሸጠው እገሌ ነው፥ የምትል ብጣቂ ወረቀት ተጥላ ተገኘች። ወረቀቷ ሌባውን ከማጋለጥዋ ሌላ “ ማን ጻፈሽ እንጃ፥ ከየት መጣሽ ከየነጃ” የምትል ነበረች። የነጃ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በወድላ ድላንታ የሚገኝ ታላቅ ደብር ነው። በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ማእበል፧ ገሞራው፣ መብረቅ፧ ነጎድጓድ ወዘተ የሚባል የቅጽል ስም የሚሰጣቸው ምሁራን ቢኖሩም ከስማቸው ጋር እንጂ እንደዚህ እንዳሁኑ ስውር ስም አልነበርም። ቤተ ክርስቲያን በድርሳናቱና በስንክሳሩ ሁሉ አጽፋ የምታስነብበን » ለዘ ጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ፧ ለዘአንበቦ ወለዘተርጎሞ በልሳን ሀዲስ፧ ወለሰማአ ቃሎ በእዝነ መንፈስ......ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ አራቂተ ኩሉ እምባእስ።» በዘመነ ጡመራ ክርታስ የሚለውን ጦማር ብለን እንተርጉመውና » በጦማር የጻፈውንና ያጻፈውን፧ በአዲስ (በተለያየ) ቋንቋ አንቦ የተረጎመውን፧ ጆሮውን አቀርቅሮ ቃሉን የሰማውን፧ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጠብ ክርክር ( ከቂም በቀል) ሁሉ አርቆ ሁላችንንም በአንድነት ይቅር ይበለን።» አሜን!

መሠረታዊ በሆነው መንገድ ሰው በነፃነት አሳቡን መግለጽ እንዳለበት ከሚያምኑ አንዱ ነኝ ብዬ አምናለሁ። ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት »የዳንኤል እይታዎች» በሚለው ጡመራ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚያዘጋጀውን ሁሉ አደንቃለሁ። » ማን ጻፈሽ እንጃ፥ ከየት መጣሽ ከየነጃ » ግን ለጊዜው መልካም መስሎ ቢታይም ውሎ አድሮ ግን ዲያብሎስ በእባቢቱ አድሮ ሔዋንን እንዳሳታት ሁሉ፧ መርገሙም ለትውልደ ትውልድ እንደተላለፈ ሁሉ ሂደቱ ጠበንጃ ( ጠብ መንጃ) መሆኑ አይቀሬ ነው። ባለፈው እና በዚህ ዓመት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ በስውር ብዕር የወጡ መጣጥፎች ቤተ ክርስቲያናችንን ምን ያህል እንደጎዱ ልብ ይሏል። የሽምቅ ውጊያ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አይፈቀድም። የሃይማኖቱን መዋቅር እንዳለ ይደመስሰዋል። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስንም እንደ መቅደም ያስቆጥራል። ለአጽራረ ቤተ ክርስቲያንም በርን መክፈት ነው። ዉጊያው ከሥጋዊውና ከደማዊው ጋር እስከሆነ ድረስ ፊት ለፊት መዋጋት ነው። ከፈሩም ከውጊያው ቀጠና ፈቀቅ ማለት ያስፈልጋል። በስውር የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አታሳየን እያሉ መጸለይ ግን ተገቢ ነው። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ » አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ፥ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፥ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሃል።» ይላልና (ማቴ.6. 6) ቤተ ክርስቲያን የማን ናት? የሚል ጥያቄ አንሥተን፧ እያንዳንዳችን ግዴታች ከተወጣን በኋላ መልሱ የሁላችን ናት ከሆነ የሰማይ መላእክት፥ የምድር ሠራዊት ሊያነዋውጥዋት አይችሉም።

4. ሐውልት እና ቤተ ክርስቲያን

ከፓትርያርኩ በዓለ ሲመት ዋዜማ ከሐምሌ 4 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሐውልት፧ ይቆማል አይቆምም የሚል ክርክር መነሣት ያለበት አይመስለንም። ዶግማውን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለይተን የማናውቅ ከሆነ፧ ያለ ዶግማ በቀር ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደ ዘመኑና እንደ ጊዜው ሊቀነስ ወይም ሊጨመር ይችላል። እንዴት የሚል ካለ ወደ ፊት ከነማስረጃው ማብራራት ይቻላል። ዋናዉ ጉዳያችን ይህ አይደለምና።

ካለፉት ወራት አንስቶ የሚያነጋግረን የሃይማኖት አባቶችን ያዉም ራሳቸዉን እንደ ሐዋርያት ዝቅ አድርገዉ በእምነት ቀበቶ አንጀታቸዉን ታጥቀዉ መንፈሳዊነት ሊሰብኩንና፤ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስም «በጎቼን ጠብቅ ግልገሎቼን አሰማራ፤ በምድር ያሰርከዉ በሰማይ የታሰረ፤ በምድርም የፈታኸዉ በሰማይ የተፈታ ይሁን።» የሚለዉን መለኮታዊ ኃላፊነት ለተሸከሙት የዓለም እዉቅናና የምድር ማስታወሻ ለምናቸዉ ነዉ?! አሁን ይህ ጥያቄ መቅረብ ያለበት እሳቸዉ አዉቀዉትም ይሁን ከእዉቅናቸዉ ዉጪ ሐውልቱ ለቆመላ(ባ)ቸው፧ ምስሎቻቸው በየቤተ ኮርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት ለተሰቀሉላ(ባ)ቸው ፓትርያርክ፤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ብቻ ነው። ሌሎች በአባታችን ላይ «ዶሮን ሲደልሏት በመጫኛ ጣሏት» እንደ ሚባለው አድርገውባቸው ከሆነ አሁንም አለመሸም ብርሃኑ እያለ ማስተከካከል ይቻላል። በቤተ ክርስቲያናችን «የቁም ፍትሐት» እንጂ የቁም ሐውልት አይታወቅምና።

ምንአልባት ሊቁ ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ ምስላቸውን እያሳዩ «አንጋረ ፈላስፋ» በተባለ መጽሐፋቸው የደረደሯቸው የሰምና ወርቅ ሥንኞች ትዝ ብለዋቸው ይሆን? የግጥሞቹ ሐረጎች እንደዚህ ይነበባሉ።
ያልሞተ ሰው የሚንቀሳቀስ ሬሳ ነው፣
ሥዕል ግን የማይንቀሳቀስ ሕያው ነው።

ሰውና ሥዕል፧ አካልና ምስል።

ከሰው ጉልበት የሥዕል ጉልበት ይበልጣል፧
ሰውዬው ሲጋደም እርሱ ጠጋ ብሎ ይቀመጣል።

ሥዕሌ ሆይ! ከእኔ ዕድሜ ያንተ ዕድሜ ይረዝማል፧
እኔ ስሞት ያንተ መሰንበት ይገርማል።

ሰላምታዬን አቅርብልኝ ለመጭው ትውልድ
አንተ ሰንባች ነህና እኔ አፈርዋናት ስኼድ።

(አፈርዋናት ገላውዴዎስ በሰሙ ወይም በቁሙ በድሮው በጌምድር በአሁኑ የዞን አከፋፈል በደቡብ ጎንደር የሚገኝ የአገር ስም ነው፥ በወርቁ ግን እኔ አፈር ስሆን፧ ስሞት፧ ስፈርስ ስበሰብስ ለማለት ነው።)
ቤተ ክርስቲያናችን ለፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን በሕይወተ ሥጋ እያሉ ዕለት በዕለት፤ ከዓመት እስከ ዓመት «ክቡር የሚሆን የጳጳሳቱን አለቃ አባ ጳውሎስን አስበው። አምላካችን ሆይ! ለብዙ ዘመናት፧ ለረጅም ወራት በእውነተና በሰላም መጠበቅን ጠብቅልን።» እያለች ትጸልያለች።
( መጽሐፈ ቅዳሴ ክፍል ጸሎተ ንስሐ ቁጥር 75-76) ቤተ ክርስቲያን በመዓርግና በቅድስና ብፁዕ ወቅዱስ ብላ ሌት ከቀን የምትጠራው አባት ለመንጋዎቹ ቸር፤ ርኅሩህ፤ እውነተኛና ሰላማዊ ጠባቂ ሆኖ መገኘት እንዳለበት እምነቱና ኃላፊነቱ ግድ ይለዋል። ከመዓርጉና ከቅድስናው ባሻገር ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ም/ቤት ፕሬዚደንት፤ የዓለም ሃይማኖቶችና የሰላም የክብር ፕሬዚደንት ተብሎ የሚጠራ አባት በዚያው ልክ እንደየመዓረጋቱ ኃላፊነቱ ሊከብደዉና ሊሰማው ይገባል። እኛ «አምላካችን ሆይ! ለብዙ ዘመናት፤ ለረጅም ወራት በእውነትና በሰላም መጠበቅን ጠብቅልን።» እያልን ስንጸልይ እርሳቸው ቸርና ርኅሩህ፤ እውነተኛና ሰላማዊ ጠባቂ፤ መሆን አቅቷቸው ከሞት በኋላ ስለሚቆም ሐውልት ምን አስጨነቃቸው? ይህ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ጥያቄ ነዉ። እናም በመዲና አዲስ አበባ፤ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ሰዉ ያየዉ፧ ፀሐይ የሞቀዉ፧ ላልሞቱት አባት የቆመዉ ሐውልት በቀጥታ የሚመለከተው ቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን ቅዱስነታቸውን ብቻ ነው እና መልሱን ከቅዱስነታቸው እንጠብቃለን።

ያለፈዉ አለፈ፤ የተሠራም ተሠራ፤ ነገር ግን የቅዱስ ሲኖዶሱን ዓመታዊ ጉባኤ ተከትሎ የተነጋገሩባቸዉን ዓበይት ጉዳዮችም ተንተርሶ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተላለፈዉ ዉሳኔ እንደዋዛ መዘለሉ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አነጋጋሪም ነዉ። እናም ቅዱስነታቸው ዘውዱን ለጫነላጨው፧ አርዌ ብርቱን ላስጨበጣቸው፧ በመንፈስ ቅዱስ ለሚመራው ለቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ አልገዛም በማለት፧ (የአበው አነጋገር » ሲገዙ ይገዙ») በማን አለብኝነት ቤተ ክርስቲያናችንን የወላድ መካን ሲያደርግዋት ዝም ብለን ልንመለከት አይገባም። የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እያደነቅን ለአፈጻጸሙ ግን እንደ ቤተ ክርስቲን ልጅነታችን ሁላችንም ድምፃችንን ልናሰማ ይገባል። «ብዙዎች ያቸንፋሉ።» የሚለው ዳዊት ደገማም ቦታው ከዚህ ላይ ነው።

ቅዱስ ሲኖዶስ ስለት ሰሚ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳይ ፈጻሚና አስፈፋሚ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል። ስለት ሰሚ ያልኩበትን ምክንያት ልገልጽ እወዳለሁ። ዘመኑ በመናኙ አባት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ፕትርክና ነው። አንድ በጎ አድራጊ ቅዱስ ሲኖዶስ እየተባለ እንደነ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ስሙ ሲጠራ በመስማቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የበግ ስለት ይዞ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ግቢ ይመጣና »ስለቴን ተቀበሉኝ» ይላል። » የምን ስለት» ብለው ሲጠይቁት » የቅዱስ ሲኖዶስ » ይላቸዋል። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም በጉን ተቀብለው ታርዶ እንዲበላ አድርገዋል። ከዚህ ላይ በጉ ለምን ታርዶ ተበላ ሳይሆን በታቦትና በሲኖዶስ መካከል ያለውን ልዩነት እዝበ ክርስቲያኑ እንዲያውቅ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል።

ነቢዩ ኢሳይያስ «ኑና አንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ
አመዳይ ትነጻለች። እንደ ደምም ብትቀላ፤ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፥ እንቢ ብትሉ ግን ብታምጹም ሰይፍ ይበላችኋል። የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።» (ኢሳ.1.18-20) ያለዉን፤ ይህን ሁለት ስለት ያለው ሰይፍ ያለውን፧ አንዱ ለምሕረት፧ ሌላው ለመዓት የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ስጠቅስ እራሴን ነፃ በማድረግ ሳይሆን አኔም እንደ አቅሚቴ ተጠያቂ መሆኔን እገነዘባለሁ። ቅዱሱ አባታችንም እኛ ልጆቻቸውን በአንድ ድምፅ «ፍረዱልኝ ወይም ፍረዱብኝ» ሊሉን ይገባል። ምናልባት፧ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን የሥልጣን አቻቸውን የሮሙን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አይሳሳትም የሚለዉን ብሂል ተከትለው ከሆነ «ቆቅ ወዲህ፧ ምዝግዝግ ወዲያ» እንደሚባለው ሆኗል ማለት ነው። የሮሙ ፓፓ አይሳሳትም የሚባለው መጀመሪያ በአማኞቹ ቀጥሎም በካህናቱና በሊቃውንቱ ብሎም በካርዲናሎቹ የተጠናውን ወደ ሃይማኖት ክፍል ይመራዋል። ያም የሃይማኖት ክፍል ቃል በቃል ወይም እንድ በአንድ ከመረመረና ካጠና ከአስተካከለም በኋላ ወደ ጠቅላላው የሲኖዶስ ጽ/ቤት ይመራዋል። ከዚህ በኋላ ፓፓው ከካርዲናሎቹ ጋር ባንድ ድምፅ የጸደቀውን ሕግ አድርጎ ያውጀዋል። አይሳሳትም የሚባለው ተመክሮ ተዘክሮበት በወጣው ሕግ እንጂ በግሉ ዕለት ከዕለት ከሚፈጽመው በደል አይደልም። እንዲያውም ፓፓው እንደ «አባታችን ሆይ» በዕለት ከዕለት ጸሎቱ ሦስት ጊዜ «እኔ በደለኛ ነኝ፥ እኔ በደለኛ ነኝ፥ እኔ በደለኛ ነኝ።» የሚለውን የንስሐ ጸሎት ሳይደግም ወደ ሌላው የጸሎት ክፍል አይሸጋገርም። የእኛ አባቶች «አቤቱ እሊህን ባሮችህን አባቶቸንና ወንድሞቼን፧ እኅቶቼንም አጽንተህ ጠብቃቸው።» ብለው ከጸለዩልን በኋላ «ዳግመኛም ኃጥእ በደለኛ የምሆን እኔንም ወራዳነቴን አይተህ ፍታኝ።» የሚለውን በአጽንዖት ደግመዉ ደጋግመዉ እየጸለዩ፤ በልቦናቸዉም እያንሰላሰሉ በመጸለይ፤ እኛም እንድንጸልየዉ አሳይተዉናልና ልንከተለዉ ይገባል። ( መጽሐፈ ቅዳሴ ክፍል ጸሎተ ንስሐ ቁጥር

82) ሁኔታውን ከዚህ ላይ በአጭሩ ልግታውና ቤተ ክርስቲያናችን የሁላችን ናት ካልን፧ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ18 ዓመት የፕትርክና ዘመን የተፈጸመውን፧ ሁሉን በመኮነን ሳይሆን፤ እውነቱን ከሐሰት፤ ሐሰቱን ከእውነት የሚለይ ክርስቲያናዊ የሆነ ብሔራዊ ጉባኤ መካሄድ ይኖርበታል ብየ አምናለሁ። እንዲሁም «አሳምናለሁ።» ጉዳዩ ትኩረትን እንዲያገኝም ጥሪዬንም አስተላልፋለሁ። እውነት አርነት ታወጣለችና። (ዮሐ. 8.32)

5. የቤተ ክርስቲያን ራእይ

ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ልወጣ አልቻልኩም፧ አሁንም ለቤተ ክርስቲያናን ራእይ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ በሁለተኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ አሥራአንድን እንድንመለከተው አሳስባለሁ። በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ዘመን የደረሰበትን ግፍና መከራ፧ ሰቆቃውና ሐዘን በብስጭት፧ እንዲያውም » እንደ እብድ ሰው እላለሁ» እያለ ከዘረዘረ በኋላ » የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው » ይላል። (1.ቆሮ.11፥28 )

በዚህ በያዝነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን እናት ቤተ ክርስቲያናችን ብሔራዊት ከመሆንዋ ባሻገር ዓለም አቀፋዊት እየሆነች በመሄድ ላይ ትገኛለች። ስንዴው እየባዛ በሄደ ቁጥር እንክራዳዱም በዚያው ልክ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ስንዴው በበዛበት አገር በኢትዮጵያ፣ በደቡብ አፍሪቃ፧ በሰሜን አሜሪካ፧ በካናዳ፧ በአውስትራልያ፧ በውሮፓ ምን እያየንና ምንስ እየሰማን ነው? ምንስ እያደረግንና ምንስ እየተደረገ ነው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ » የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው » ብሎ እንደ ጮኸው በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የማያሳስበው መሪና ተመሪ፧ ጠባቂና ተጠባቂ ካለ » እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ » አቤቱ ይቅር በለን የሚያሰኝ ነው። ራእይ የማይወሰን ቢሆንም በትንሹ ለመግለጽ፣

በእኔ እይታ በዚህ አንገብጋቢ ጊዜ ዋናው ራእይ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሚነጋገር በሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ማካሄድ ነው። በውስጡ የሚዳስሳቸው፧

1. በየቦታው ያለውን ልዩነት ለማስቀረት፣ በተለይም በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ያለውን ውግዘት ለማሥነሣት፧
2. » ውላጤ ዘእንበለ ውላጤ » ያለ ለውጥ ለውጥ ማድረግ ( ከዛሬ 48 ዓመታት በፊት የመልአከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈ ንግግር ) አሁንም ወይ ፍንክች
3. ሁሉ ሕግ ተርጓሚ በሆነበት ዘመን ፍትሐ ነገሥቱን እንደ ገና ማጥናትና መመርመር
4. ዶግማውን ከቀኖና (ውሳኔውን ከሥርዓት) መለየት፧
5. ገድላትንና ድርሳናትን፧ አዋልድ መጻሕፍትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ለይቶ ማጥናት ( አጼ ዮሐንስ በነገሡ በሁለተኛው ዓመት በ1870 ዓ.ም. ከዛሬ 133 ዓመታት በፊት በተዋሕዶና በጸጋ ልጆች መካከል በቦሩ ሜዳ በተደረገው ብሔር አቀፍ ጉባኤ የጸጋ ልጆች ሦስት ልደት ብለው ይከራከሩ ስለነበር፣ ንጉሡ » ሦስት ልደት የሚል መረጃ አቅርቡ » ብለው ሲጠይቁ አለቃ ወልደ ዮሐንስ የተባሉት ተከራካሪ » ጃንሆይ በተአምረ ማርያም ተጽፎ ይገኛል » አሉ። አጼ ዮሐንስ ግን » እርሱን ተወውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰህ ማስረጃ አቅርብ» ነው ያሏቸው። ከ133 ዓመታት በኋላ አሁን ያለውን ሁሉ ልብ ይሏል።)
6. በሥልጣነ ክህነት አሰጣጥና በጵጵስና ሹመት ላይ ጥብቅ መመዘኛ ማውጣት፣ በአንድ ጳጳስ ያውም በባ̎ዕድ፧ በገበሬ ቀሳውስትና በጨቅላ ዲያቆናት ስትገለገል ለኖረች ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ግን ከፍተኛ መመዘኛ ማውጣት የግድ ይላል። ሰለምን? በአሁኑ ጊዜ ጥቅማ ጥቅም አለና፧ ኃላፊነቱም በዚያው ልክ እየከበደ መጥቷል። ጥራት እንጂ ብዛት አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። አውደልዳይ እንዳይበዛ፧
7. የሀገረ ስብከቶችን ደረጃ መወሠን፣ ዝም ብሎ በመደዳ ሊቀ ጳጳስ ማለት ሳይሆን፥ የኢጲስቆጶስ፣ የጳጳስ ከዚያም የሊቀ ጳጳስ አመደዳደብ ኑሮ የመዓርግ ውረድ ተዋረድ ያስፈልጋል።
8. የመንፈሳዊ አገልግሎትን ጊዜ መወሠን፥ ከ-እስከ የሚል ገደብ ሊኖር ይገባል። በተለይ የከተማው ኗሪ ሕዝበ ክርስቲያን ሥራው ከሰዓት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ በጥብቅ የሚታሰብበት ጉዳይ ነው።
9. በከተማ በሚገኙ ገዳማት ሕጋውያን ቀሳውስት እንዲቀድሱባቸውና እንዲሾሙባቸው ማድረግ፧ በቀሳውስትና በመነኮሳት መካከል ምንም ዓይነት የሥልጣነ ክህነት ልዩነት የለምና፣
10. ገዳማት ወደ ጥንቱ ሥርዓት ተመልሰው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲረዱ መልሶ ማቋቋም፥ መነኮሳትና መነኮሳያት ከአበ ምኔቱና ከእመ ምኔቷ ፈቃድ ሳይዙ ወደ ከተማ እንዳይገቡ ማድረግ፧
11. የአብነት ትምህርት ቤቶች ምንጭ እንዳይደርቅ ለመምህራንና ለተማሪዎች በጀት መመደብ፧ ራእዩ ቀላል ቢሆንም በሥራ መተርጎሙ ይከብድ ይሆናል። ሆኖም እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ካለው ገቢ የተወሠነውን % ከከፈል በሥራ የማይተረጎምበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።
12. አማርኛ ወዘተ ( ቋንቋ ) የተናገረ ሁሉ ሰባኬ ወንጌል መሆን ስለማይችል ልዩ ማሰልጠኛ ማዘጋጀት፧ ይህ ማሰልጠኛ የቤተ ክርስቲያኗ የሙያ ሠራተኞችም የሚሠለጥኑበት ሊሆን ይችላል።
13. የሴቶችን ተሳትፎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማጠናከር፥ በዓለም ላይ በሴቶች መብዓ እንጂ በጉልበታቸው፥ በእውቀታቸውና በኃይላቸው የማትጠቀም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት። በዓለም ክርስቲያኖችም ዘንድ መዘባበቻ ሁናለች።
14. ጠቅላይ ቤተ ክህነት የተቋቋመው በቤተ መንግሥት አንጻር አስተዳደሩን ለመምራት እሰከ ሆነ ድረስ ሊቃነ ጳጳሳት እንደ ጽዋ ማኅበር »ማነህ ባለሳምንት» እየተባባሉ የሚቀበሉት ሹመት መሆን የለበትም፧ ለአስስተዳዳሪነት በቂ ሆኖ ከተገኘ ሊቀ ጳጳስ፧ ካህን በመነኮሳቱ አጠራር ጥቁር ራስ፧ መነኮስ፧ ምእመን ሊሆን ይችላል።
15. የሌሎች ሃይማኖቶችን ሂደት የሚከታተል ክፍል ማቋቋም፧
» የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው »መርዓዊ ተበጀ